Wednesday, September 30, 2009

እውነቱ ሲነገረው የማይወድ የሀሰት ልጅ ነው

እውነቱ ሲነገራችሁ እውነቱን የነገራችሁን ቶሎ ብላችሁ አንባቢን ለማወናበድ እንደለመዳችሁት የማታውቁትን ሰው ደስ ያላችሁን ስም ይልቁንም ለናንተ የሚስማማውን ስም ትቀባላችሁ።

እኔ ንጹህ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጅ ነኝ። ተሀድሶም አላልኩም ወይም መናፍቅ ሆኜ አላውቅም። በሐይማኖቴ ጸንቼ ያለሁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከአባቶች እግር ስር ቁጭ ብዬ የምማር፤ ሳይገባኝ ግን በቸርነቱ ብዛት በቤቱ የማድግና እንደ አቅሜ የማገለግል ብላቴና ነኝ።

ይልቁን የሚታደሰው በአመጻ የደነደነ ተሳዳቢ፣ ሸረኛ፣ የማያምን ግን በአማኞች መካከል አማኝ መስሎ አመጻን የሚያስነሳ ልብ ነው። ለምሳሌ የዘመኑ ፈሪሳዊያኖች ማህበረ ሰይጣኖች፤ በአማኞችና በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱ ናቸው።

«የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።» ሮሜ 12፥2

በጎና ደስ የሚያሰኘውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በአመጻ፣ በስድብ፣ ጳጳሳትንና አበው ካህናትን በመሳደብ ልታውቁ የምትደክሙ የጥፋት መልእክተኞችን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንን ዓለም አትምሰሉ አለ። ከአመጻ እራስን ዝቅ ወደማድረግ፣ ጳጳሳትንና አበው ካህናትን ከመሳደብ ማክበርና ብሎም እግራቸው ስር ቁጭ ብሎ መማር። የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው አለ እንጂ ስደቧቸው ወይም በሀሰት ክሰሷቸው የሚል ቃል የለም። ካለ እስኪ እዚህ ጋር ይገኛል በሉን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ፈቅዶልን ነው በሉን።

የምትሳደቡት ግን ከልባችሁ ሞልቶ የተረፈ የአመጻ ፍሬያችሁ ስለሆነ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፥

«ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ።» የማቴዎስ ወንጌል 12፥33-38

ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንን ዓለም አትምሰሉ ያለው። ልባችሁ ታድሶ መልካም ፍሬን ቢያፈራ ኖሮ ቀና ብላችሁ በድፍረት የሐይማኖት አባቶችን ባልተሳደባችሁ ነበር። ያለ ስልጣናችሁም መናፍቅ የሚል ስም ባልቀባችኋቸው ነበር። እነርሱ ይህ አይደንቃቸውም ሊቀ ካህናቱም(ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም) ይህንኑ ተብሎ ተሰድቧልና ለነሱ ስለ እውነት መሰደብ ክብር ነው። «ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።» የማቴዎስ ወንጌል 5፥11፡12 ከዝንብ ማር አንጠብቅም እንዲሉ አበው፤ ልባችሁ ያላፈራውን እንዴት ከአንደበታችሁ ይጠበቃል።

አሁንም እላለሁ!!! በፍርድ ቀን ነጭ ልብስ ለብሳችሁ የነፍሳችሁን ቤዛ በደስታና በዝማሬ ለመቀበል የምትሹ ሁሉ የንስሃ ጊዜ ዛሬ አይደለም ግን አሁን አዎን አሁን ነው። ነገ የኛ ለመሆኗ ምንም ዋስትና የለምንም። ክርክሩን ትተን በንስሃ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንቅረብ። ድህነት የሚገኘው በአድመኝነት፣ በአመጻ፣ በስድብ፣ በተንኮል፣ ንዑሰ ክርስቲያኖችን በማታለል፣ በአጠቃላይ በክፉ ፍሬ አይደለም። በንስሀ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ብቻ ነው።

ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይላል፥

ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ።
ወኢይትኀፈር ገጽክሙ።
ዝንቱ ነዳይ ጸርኀ ወእግዚአብሔር ሰምዖ።

ትርጉም፥
ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል
ፊታችሁም አያፍርም።
ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚአብሔርም ሰማው።
መዝሙር 33፥5

Tuesday, September 29, 2009

የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ

የሚገርመው ነገር «መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ» እንዲሉ እነዚህ እራሳቸውን ማህበረ ቅዱሳን እያሉ የሚጠሩ ማህበረ ሰይጣኖች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስር ነን እያሉ እንደ መዥገር ተለጥፈው ንጹሐን ወንድሞችንና እህቶችን በማሳሳት አባቶችን እንዲሳደቡ የሚያደርጉ አንዴ በቅዱሳን ስም እራሳቸውን ማህበረ ቅዱሳን ደግሞም የጥፋት መልእክተኞች እንደሆኑ እያወቅናቸው እራሳቸውን በሌላ ስም ደጀ ሰላም ብለው አሁንም የማጭበርበር ሥራቸውን እንደ ቀጠሉ አሉ። እኔን የሚያሳዝነኝ ግን እነሱ ለነፍሳቸው የማይራሩ መሆናቸውና እንደ ድሮው ባይሆንም አሁንም ድረስ በነዚህ ማህበረ ሰይጣኖች የሚታለሉት ወንድሞችና እህቶች ናቸው።


«አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም» እንዲሉ ለማህበሩ መሪዎች ነን ለሚሉት በመምከር ጊዜዬን አላጠፋም። በፍጹም ልባቸው እግዚአብሔርን ብለው ይቅርታ ለማግኘትና ላደረገላቸው ነገር ምስጋና ለማቅረብ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሚመጡ በደመ ክርስቶስ የከበሩ ንጹሐን ወንድሞችና እህቶች ግን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሼ ለማለፍ እወዳለሁ፥


«የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።» ወደ ዕብራውያን 1378


ቅዱስ ቃሉ «ዋኖቻችሁን» የሚለው ሰላም ለኪ ሳይሉና ሀብተ ክህነት ሳይኖራቸው በራሳቸው ፈቃድ በቅዱሳን ስም ማህበር አቋቁመው አስራት የሚሰበስቡትን ሳይሆን በነ ቅዱስ ጴጥሮስ ወንበር የተተኩትን ቅዱሳን አባቶችን እንደሆነ ይህን እውነት መገንዘብ የሚያስቸግራችሁ አይመስለኝም። እባካችሁ የነፍሳችሁ ቤዛ ወደሆነው ወደጌታችንና ወደመድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልከቱ። እግዚአብሔር አምላክ በቅዱስ ልጁ የጠራን ለአመጻ ሳይሆን ለመዳንና ብሎም ለኛ ያዘጋጀልንን ሰማያዊ ቤት ለማውረስ ነው። ይህ ደግሞ በአመጻ፣ አበውን በመሳደብና በማዋረድ የሚገኝ አይደለም። እባካችሁ እናስተውል። ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት የመናፍቅና የኢአማንያን ሳይበቃ እኛ ገና ለእምነቱ ሕጻናት የሆነው ለአባቶች ህመም አንሁንባቸው። ሁሉን ትታችሁ አበውን ጠይቁ ንጹሁን እምነታችንን ያስተምሩዋችኋል። እራሳቸውን ለዚህ ቅዱስ አገልግሎት አሳልፈው የሰጡ ቅዱሳን አባቶች በክርስቶስ ፍቅርና ትህትና ያስተምሩናል። የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። የእግዚአብሔርን ስም እየጠሩ በግብራቸው የካዱትን ሳይሆን በኑሮአቸው የሚመስሉትን ምሰሉ።

«ማህበረ ቅዱሳን ወይስ ማህበረ ሰይጣን» የሚለውን መጽሐፍ እንዴት ይመለከቱታል?

«ማህበረ ቅዱሳን ወይስ ማህበረ ሰይጣን» በዲያቆን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል፤ በሚለው መጽሐፍ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? ብዙ በፊርማና በማህተም የተረጋገጡ ማስረጃዎች አሉት፤ እና እንዴት ይመለከቱታል? ካላነበቡት ይህን ሊንክ ይመልከቱ http://www.thetruthfighter.net/

Saturday, September 12, 2009

እውነቱን ተናግሮ ካመሹበት ማደር

ማህበረ ቅዱሳን ማን ነው? ከየት መጣ? በማንስ ተመሰረተ? አላማውስ ምንድን ነው? በአሁን ወቅትስ ምን እያደረገ ይገኛል? የሚያውቁትን እውነት በማሳወቅ ቤተ ክርስቲያናችንን እናድን።